1 ነገሥት 21:10-16 NASV

10 እንዲሁም ሁለት የሐሰት ምስክሮች ከፊት ለፊቱ አስቀምጡና፣ ‘እግዚአብሔርንም ንጉሡንም ሰድቦአል’ ብለው ይመስክሩበት፤ ከዚያም አውጥታችሁ በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉት።”

11 ስለዚህ በናቡቴ ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት በደብዳቤዎቹ ላይ እንደ ጻፈችላቸው አደረጉ።

12 የአንድ ቀን ጾም ዐወጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀመጡት።

13 ከዚያም ሁለት የሐሰት ምስክሮች መጥተው ከፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ በሕዝቡም ፊት፣ “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል” ብለው መሰከሩበት። ስለዚህ ከከተማዪቱ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወግረው ገደሉት።

14 ከዚያም ለኤልዛቤል፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶአል” ብለው ላኩባት።

15 ኤልዛቤልም በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን ወዲያው እንደ ሰማች አክዓብን፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶአል፤ በል ተነሣና ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ውሰደው” አለችው።

16 አክዓብ የናቡቴን ሞት ሲሰማ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ተነሥቶ ወረደ።