18 “ተነሣና በሰማርያ ሆኖ የሚገዛውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ሄዶ አሁን እዚያው ይገኛል።
19 እንዲህም በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰውየውን ገደልኸው፤ ደግሞ ርስቱን ልትወስድ? ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ውሾች እንዲሁ ይልሱታል!’ ”
20 አክዓብም ኤልያስን፣ “ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?” አለው።ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “በእግዚአብሔር ፊት የተጠላውን ነገር ለማድረግ ራስህን ሸጠሃልና አዎን አግኝቼሃለሁ።
21 ‘እነሆ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፤ ዘርህን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ እያንዳንዱን የአክዓብን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ከእስራኤል እጠርጋለሁ።
22 ለቊጣ ስላነሣ ሣኸኝና እስራኤልንም ስላሳትሃቸው ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።’
23 “ስለ ኤልዛቤልም እግዚአብሔር፣ ‘በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ውሾች ኤልዛቤልን ይበሏታል’ ይላል።
24 “ደግሞም ከአክዓብ ወገን ሆኖ በከተማ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በገጠር የሞተውንም የሰማይ አሞሮች ይበሉታል።”