6 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ልዝመት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።
7 ኢዮሣፍጥ ግን፣ “የምንጠይቀው የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።
8 የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ አንዳችም መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ ይህም ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” ሲል መለሰ።
9 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “በል የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።
10 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር አጠገብ ባለው አውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው ሳለ፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።
11 በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ የተባለው የክንዓና ልጅ የብረት ቀንዶች አበጅቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ የምትወጋቸው በእነዚህ ነው’ ” አለው።
12 የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና በገለዓድ የምትገኘውን ሬማትን ወግተህ ድል አድርግ” በማለት በአንድ ቃል ትንቢት ይናገሩ ነበር።