1 ነገሥት 7:25-31 NASV

25 ገንዳውም፣ ሦስቱ ፊታቸውን ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ባዞሩ የዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ገንዳው በላያቸው ሆኖ የሁሉም የኋላ አካል በመካከል ላይ የገጠመ ነበር።

26 የገንዳው ውፍረት አንድ ጋት ሲሆን፣ የከንፈሩ ጠርዝ ደግሞ እንደ አበባ ቅርጽ ሆኖ፣ የጽዋ ከንፈር የመሰለ ነው፤ ይህም አርባ ሁለት ሺህ ሊትር ያህል ውሃ የሚይዝ ነበር።

27 እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዐሥር ባለ መንኰራኵር የዕቃ ማስቀመጫዎች ከመዳብ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ርዝመት አራት ክንድ፣ ወርድ አራት ክንድ፣ ቁመትም ሦስት ክንድ ነበር።

28 የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ባለ አራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው።

29 ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኮርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኮርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጒንጒን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ።

30 እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጒንጒን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው።

31 በዕቃ ማስቀመጫወቹም ውስጥ ጥልቀቱ አንድ ክንድ የሆነ ባለ ክብ ክፍተት ነበር፤ ይህም ክፍተት ድቡልቡል ሆኖ ከታች ከመቆሚያው በኩል ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ወርድ ሲኖረው፣ በክፍተቱም ዙሪያ ቅርጾች ነበሩ፤ ክፈፎቹ ግን ባለ አራት ማእዘን እንጂ ክብ አልነበሩም።