58 በመንገዱም ሁሉ እንድንሄድ፣ ለአባቶቻችን የሰጣቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ደንቦች እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እርሱ ይመልስ።
59 በየዕለቱም ባሪያውንና ሕዝቡን እስራኤልን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲረዳቸው፣ ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያቀረብኋት የራሴ ልመና በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት ትቅረብ።
60 ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆነና ከእርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ነው።
61 ስለዚህ እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ፣ በሥርዐቱ እንድትኖሩና ትእዛዙን እንድትጠብቁ ልባችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተገዛ ይሁን።”
62 ከዚያም ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ።
63 ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺህ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺህ በግና ፍየል የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ንጉሡና እስራኤላውያንም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በዚህ ሁኔታ ቀደሱ።
64 በዚያኑ ዕለትም ንጉሡ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የአደባባዩን መካከለኛ ክፍል ቀደሰ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህል ቊርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ አቀረበ፤ ይህን ያደረገውም በእግዚአብሔር ፊት የነበረው የናስ መሠዊያ ከትንሽነቱ የተነሣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት የእህሉን ቊርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ መያዝ ባለመቻሉ ነበር።