1 ነገሥት 9:1-7 NASV

1 ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ ከጨረሰና ለመሥራት የፈለገውንም ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣

2 እግዚአብሔር ለሰሎሞን በገባዖን ተገልጦለት እንደ ነበረ ሁሉ ዳግም ተገለጠለት።

3 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤“በፊቴ ያቀረብኸውን ጸሎትና ልመና ሰምቻለሁ፤ ይህን የሠራኸውንም ቤተ መቅደስ ስሜን በዚያ ለዘላለም እንዲኖር በማድረግ ቀድሼዋለሁ፤ ዐይኖቼና ልቤ ምንጊዜም በዚያ ይሆናሉ።

4 “አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው፣ በልበ ቅንነትና በትክክለኛነት ብትሄድ፣ የማዝህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቴንና ሕጌን ብትጠብቅ፣

5 ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ከዘርህ ሰው አታጣም’ በማለት በሰጠሁት ተስፋ መሠረት ዙፋንህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።

6 “ነገር ግን አንተም ሆንህ ልጆችህ እኔን ከመከተል ወደ ኋላ ብትመለሱ፣ የሰጠኋችሁን ትእዛዞችና ሥርዐቶች ሳትጠብቁ ብትቀሩ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩና ብትሰግዱላቸው፣

7 እኔም እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላቸዋለሁ፤ ስለ ስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስም እተወዋለሁ፤ ከዚያም እስራኤል በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ ይሆናሉ፤