1 ነገሥት 9:4-10 NASV

4 “አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው፣ በልበ ቅንነትና በትክክለኛነት ብትሄድ፣ የማዝህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቴንና ሕጌን ብትጠብቅ፣

5 ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ከዘርህ ሰው አታጣም’ በማለት በሰጠሁት ተስፋ መሠረት ዙፋንህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።

6 “ነገር ግን አንተም ሆንህ ልጆችህ እኔን ከመከተል ወደ ኋላ ብትመለሱ፣ የሰጠኋችሁን ትእዛዞችና ሥርዐቶች ሳትጠብቁ ብትቀሩ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩና ብትሰግዱላቸው፣

7 እኔም እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላቸዋለሁ፤ ስለ ስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስም እተወዋለሁ፤ ከዚያም እስራኤል በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ ይሆናሉ፤

8 ይህ ቤተ መቅደስ አሁን የሚያስገርም ቢሆንም እንኳ፣ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል፤ ዐላፊ አግዳሚውም ሁሉ ይገረማል፤ እያፌዘም፣ ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያደረገው ስለ ምን ይሆን?’ ይላል፤

9 ራሱ መልሶም፣ ‘አዎን እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው አባቶቻቸውን ከግብፅ ምድር ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎች አማልክትን በመከተል ስለ ሰገዱላቸውና ስላመለኳቸው ነው’ ይላል።”

10 ሰሎሞን ሁለቱን ሕንጻዎች፣ ማለትም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የንጉሡን ቤተ መንግሥት ሠርቶ በፈጸመ በሃያኛው ዓመት መጨረሻ፣