2 ነገሥት 13:15-21 NASV

15 ኤልሳዕም፣ “አንድ ቀስትና ፍላጾች አምጣ” አለው፤ እርሱም አመጣ፤

16 የእስራኤልንም ንጉሥ፣ “ቀስቱን በእጅህ ያዘው” አለው፤ ቀስቱን በያዘውም ጊዜ ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ።

17 ቀጥሎም፣ “የምሥራቁን መስኮት ክፈት” አለው፤ ከፈተውም፤ ኤልሳዕም፣ “በል አስፈንጥረው” አለው፤ አስፈነጠረውም፤ ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር የድል ቀስት!” ሶርያ ድል የምትሆንበት ቀስት!” አለ። ኤልሳዕም እንደ ገና “ሶርያውያንንም አፌቅ ላይ ፈጽመህ ድል ታደርጋቸዋለህ” አለው።

18 ቀጥሎም፣ “በል ቀስቶቹን ውሰድ” አለው፤ ንጉሡም ወሰደ። ኤልሳዕም፣ “መሬቱን ውጋ” አለው። እርሱም ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ።

19 የእግዚአብሔርም ሰው ተቈጣውና፣ “መሬቱን አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ነበረብህ፤ እንዲህ ብታደርግ ኖሮ ሶርያን ታሸንፍና ፈጽመህ ትደመስሳት ነበር፤ አሁን ግን የምታሸንፈው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው” አለው።

20 ኤልሳዕ ሞተ፤ ቀበሩትም። በዚህም ጊዜ ሞዓባውያን አደጋ ጣዮች በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ እስራኤል ምድር እየሰረጉ ይገቡ ነበር።

21 አንድ ጊዜ እስራኤላውያን ሰው ሞቶ ሲቀብሩ፣ አንድ የአደጋ ጣይ ቡድን በድንገት አዩ፤ ስለዚህ የሞተውን ሰው ሬሳ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ ሬሳው የኤልሳዕን ዐፅም እንደ ነካም ወዲያውኑ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ።