2 ነገሥት 13:20-25 NASV

20 ኤልሳዕ ሞተ፤ ቀበሩትም። በዚህም ጊዜ ሞዓባውያን አደጋ ጣዮች በየዓመቱ በጸደይ ወራት ወደ እስራኤል ምድር እየሰረጉ ይገቡ ነበር።

21 አንድ ጊዜ እስራኤላውያን ሰው ሞቶ ሲቀብሩ፣ አንድ የአደጋ ጣይ ቡድን በድንገት አዩ፤ ስለዚህ የሞተውን ሰው ሬሳ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ ሬሳው የኤልሳዕን ዐፅም እንደ ነካም ወዲያውኑ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ።

22 በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፣ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል፣ እስራኤልን ያስጨንቃቸው ነበር።

23 እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፤ አዘነላቸው፤ ፊቱን መለሰላቸው፤ ይህም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ስለ ገባው ኪዳን ሲል ነው፤ እስከ ዛሬ ድረስ ሊያጠፋቸው አልፈለገም፤ ከፊቱም አላስወገዳቸውም።

24 የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁ ቤንሃዳድም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

25 ከዚያም የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ፣ አዛሄል ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በጦርነት የወሰዳቸውን ከተሞች ከአዛሄል ልጅ ከቤን ሃዳድ አስመልሶ ያዘ። ዮአስ ሦስት ጊዜ ድል አደረገው፤ የእስራኤልንም ከተሞች በዚህ ሁኔታ መልሶ ያዘ።