2 ዜና መዋዕል 31:11-17 NASV

11 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ጎተራ እንዲያዘጋጁ አዘዛቸው፤ እነርሱም አዘጋጁ።

12 ከዚያም ስጦታውን፣ ዐሥራቱንና የተቀደሱ ስጦታዎቹን በታማኝነት አምጥተው አስገቡ። ሌዋዊው ኮናንያ የእነዚሁ ዕቃዎች ኀላፊ ሲሆን ወንድሙ ስሜኢ ደግሞ በማዕረግ ሁለተኛ ነበር።

13 ይሒዒል፣ ዓዛዝያ፣ ናሖት፣ አሣሄል፣ ይሬሞት፣ ዮዛባት፣ ኤሊኤል፣ ሰማኪያ፣ መሐትና በናያስ በንጉሡ ሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ በዓዛርያስ ተሹመው በኮናንያና በወንድሙ በሰሜኢ ሥር ሆነው ተቈጣጣሪዎች ነበሩ።

14 የምሥራቁ በር ጠባቂ የሆነው የሌዋዊው የይምና ልጅ፣ ቆሬ ደግሞ በበጎ ፈቃድ፣ ለእግዚአብሔር በቀረበው ስጦታ ላይ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትንም ነገሮች ለማከፋፈል፣ ኀላፊ ነበረ።

15 ዔድን፣ ሚንያሚን፣ ኢያሱ፣ ሸማያ፣ አማርያና ሴኬንያ በካህናቱ ከተሞች ተገኝተው፣ ለካህናት ወገኖቻቸው ለታላላቆቹም ሆነ ለታናናሾቹ፣ እንደየምድባቸው፣ በማከፋፈሉ ረገድ በታማኝነት ረዱት።

16 በተጨማሪም፣ ስማቸው በትውልድ መዝገቡ ውስጥ የነበረና የየዕለቱ ልዩ ልዩ ተግባራቸውን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው ለማከናወን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት ለሚችሉት፣ ዕድሜአቸው ሦስት ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ወንዶች ልጆች እንደዚሁ አከፋፈሉ።

17 በትውልድ መዝገብ በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ለገቡት ካህናት፣ ዕድሜአቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ሌዋውያን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው አካፈሏቸው።