1 ኢያሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን ቀድሞ ይውጣልን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።
2 እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ፤ እነሆ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ” በማለት መለሰ።
3 የይሁዳም ሰዎች ወንድሞቻቸውን የስምዖንን ልጆች፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ድርሻችን ወደ ሆነው ምድር አብረን እንውጣ፤ እኛም እንደዚሁ ድርሻችሁ ወደ ሆነው ምድር አብረናችሁ እንወጣለን” አሏቸው፤ ስለዚህም የስምዖን ሰዎች አብረዋቸው ሄዱ።
4 ይሁዳ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ላይ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ ቤዜቅ በተባለውም ስፍራ ዐሥር ሺህ ሰው ገደሉ።
5 በዚህም ኦዶኒቤዜቅን አግኝተው ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን ድል አደረጉ።
6 አዶኒቤዜቅም ከዚያ ሸሸ፤ እነርሱ ግን አሳደው ያዙት፤ የእጆቹንና የእግሮቹንም አውራ ጣቶች ቈረጡ።