መሳፍንት 1:14-20 NASV

14 እርሷም ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜ፣ አባቷ የዕርሻ መሬት እንዲሰጠው ይለምነው ዘንድ አጥብቃ ነገረችው፤ ካሌብም እርሷ ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

15 እርሷም፣ “እባክህ አንድ ነገር አድርግልኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።

16 የቄናዊው የሙሴ ዐማት ዝርያዎች ከዓራድ አጠገብ በኔጌብ ውስጥ በይሁዳ ምድረ በዳ ካሉት ሕዝቦች ጋር አብረው ለመኖር፣ ከይሁዳ ሰዎች ጋር በመሆን ከባለ ዘንባባዋ ከተማ ከኢያሪኮ ወጡ።

17 የይሁዳ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ከስምዖን ልጆች ጋር ሆነው በጻፋት በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ከተማዪቱንም ፈጽሞ ደመሰሷት፤ ስለዚህ ከተማዪቱ ሔርማ ተብላ ተጠራች።

18 ደግሞም የይሁዳ ሰዎች ጋዛ፣ አስቀሎና፣ አቃሮን የተባሉትን ከተሞች ከነግዛቶቻቸው ያዙ።

19 እግዚአብሔር ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኰረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለ ነበሯቸው ከዚያ አሳደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም።

20 ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች፤ እርሱም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች ከውስጧ አሳደደ።