1 ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ኀያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች።
2 እንደዚሁም የገለዓድ ሚስት ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፣ “ከሌላ ሴት ስለ ተወለድህ ከቤተ ሰባችን ምንም ዐይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት።
3 ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት።
4 ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፣
5 የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ።
6 እነርሱም፣ “ከአሞናውያን ጋር መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት።
7 ዮፍታሔም፣ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው።