መሳፍንት 11:20-26 NASV

20 ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሰራዊቱንም ሰብስቦ በያሃድ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ።

21 “ከዚያም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ አሸነፏቸውም፤ እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤

22 ከአርኖን እስከ ያቦቅ፣ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ወረሱ።

23 እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳዶ ካስወጣቸው፣ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ?

24 አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ ነው፤ እኛም እንደዚሁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን እንወርሳለን።

25 አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋር ተጣልቶአልን? ወይስ ተዋግቶአልን?

26 እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮቿ፣ በአሮዔርና በመንደሮቿ፣ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያን ጊዜ ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር?