መሳፍንት 11:29-35 NASV

29 ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ፤ ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው።

30 ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣

31 አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።”

32 ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ እግዚአብሔርም እርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው።

33 ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባቢ ከዚያም አልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ።

34 ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም።

35 ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፣ “ወይኔ ልጄ ጒድ አደረግሽኝ! ጭንቅም ላይ ጣልሺኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁና” ብሎ በኀዘን ጮኸ።