1 እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት እንዲገዙ አሳልፎ ሰጣቸው።
2 ማኑሄ የተባለ ከዳን ወገን የተወለደ አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስቱ መካን ስለ ነበረች ልጅ አልወለደችም።
3 የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ አንቺ መካን ነሽ፤ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።
4 እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኵስ ነገርም አትብዪ፤