መሳፍንት 14:1-7 NASV

1 ሳምሶን ወደ ተምና ወረደ፤ እዚያም አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አየ።

2 እንደተመለሰም አባቱንና እናቱን፣ “በተምና አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አይቻለሁና አሁኑኑ አጋቡኝ” አላቸው።

3 አባቱና እናቱም፣ “ከዘመዶችህ ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት መች ታጣችና ነው ወዳልተገረዙት ፍልስጥኤማውያን ሚስት ፍለጋ የሄድኸው?” አሉት።ሳምሶንም አባቱን፣ “ልቤን የማረከችው እርሷ ናትና እርሷን አጋባኝ” አለው።

4 በዚያን ጊዜ በእስራኤል ላይ ገዦቹ ፍልስጥኤማውያን ስለ ነበሩ፣ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር እግዚአብሔር ሆን ብሎ ያደረገው ነገር መሆኑን አባቱና እናቱ አላወቁም ነበር።

5 ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናንቱ ጋር ወደ ተምና ወረደ፤ በዚያም ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፣ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት።

6 በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ስለዚህ የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል አንበሳውን ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጠለው፤ ያደረገውን ግን ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም ነበር።

7 ወደ ሴቲቱም ወረደ፤ ከእርሷም ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ወደዳት።