መሳፍንት 14:5-11 NASV

5 ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናንቱ ጋር ወደ ተምና ወረደ፤ በዚያም ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፣ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት።

6 በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ስለዚህ የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል አንበሳውን ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጠለው፤ ያደረገውን ግን ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም ነበር።

7 ወደ ሴቲቱም ወረደ፤ ከእርሷም ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ወደዳት።

8 ከጥቂት ቀን በኋላም ሊያገባት ተመለሰ፤ የአንበሳውንም በድን ለማየት ከመንገድ ዘወር አለ፤ በበድኑም ውስጥ የንብ መንጋ ሰፍሮ ተመለከተ፤ ማርም ነበረበት፤

9 በእጁ ወስዶም መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ከወላጆቹም ጋር እንደተገናኘም ከማሩ ሰጣቸው፤ እነርሱም በሉ። ነገር ግን ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን መሆኑን አልነገራቸውም ነበር።

10 የሳምሶን አባት ልጅቱን ሊያይ ወረደ፤ ሳምሶንም በነበረው የሙሽራ ወግ መሠረት በዚያ ግብዣ አደረገ።

11 እርሱም ለፍልስጥኤማውያን በታየ ጊዜ፣ ሠላሳ አጃቢዎች ሰጡት።