መሳፍንት 16:5-11 NASV

5 የፍልስጥኤማውያን ገዦች ወደ እርሷ ሄደው፣ “እርሱን አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማዋል ልናሸንፈው እንዴት እንደምንችልና የብርታቱ ታላቅነት ምስጢር ምን እንደሆነ እንዲያሳይሽ እስቲ አባብዪው፤ ይህን ካደረግሽ እያንዳንዳችን አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ጥሬ ብር እንሰጥሻለን” አሏት።

6 ስለዚህም ደሊላ ሳምሶንን፣ “የብርታትህን ታላቅነት ምስጢርና ታስረህ በቊጥጥር ሥር የምትውለው እንዴት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው።

7 ሳምሶንም፣ “ማንም ባልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች ቢያስረኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።

8 ከዚያም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ያልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች አመጡላት፤ እርሷም አሰረችው።

9 ሰዎች በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር፤ እርሷም፣ “ሳምሶን ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው፤ ሳምሶን ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚ በጣጠስ ጠፍሮቹን በቀላሉ በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ የብርታቱ ምስጢር ምን እንደሆነ ሊታወቅ አልቻለም።

10 ደሊላም ሳምሶንን፣ “አሞኝተኸኛል፤ ዋሽተኸኛል፤ እባክህ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል ንገረኝ” አለችው።

11 እርሱም፣ ሥራ ላይ ባልዋሉ አዳዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።