መሳፍንት 17:1-7 NASV

1 ሚካ የተባለ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖር ሰው ነበር።

2 እናቱን፣ “አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ብር ተሰርቆብሽ፣ የሰረቀውን ሰው ስትራገሚ ሰምቼሽ ነበር፤ ብሩ ከእኔ ዘንድ ይገኛል፤ የወሰድሁት እኔ ነኝ” አላት።ከዚያም እናቱ፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለችው።

3 አንድ ሺህ አንድ መቶውን ሰቅል ብር በመለሰላት ጊዜ እናቱ፣ “ብሬን የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት ለማበጀት ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተው መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው።

4 ስለዚህ ብሩን ለእናቱ መለሰላት፤ እናቱም ከላዩ ሁለት መቶ ጥሬ ብር ወስዳ ለብር አንጥረኛ ሰጠች፤ አንጥረኛውም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት አደረገው፤ ምስሎቹም በሚካ ቤት ተቀመጡ።

5 ሚካ የተባለው ይህ ሰው የአምልኮ ስፍራ ነበረው፤ አንድ ኤፉድና ተራፊም ሠርቶ ከልጆቹ አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው አደረገ።

6 በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱ ሰው ለራሱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።

7 በይሁዳ ምድር፣ በይሁዳ ነገድ መካከል በቤተልሔም የሚኖር አንድ ሌዋዊ ወጣት ነበር።