መሳፍንት 18:25-31 NASV

25 የዳን ሰዎች፣ “አትሟገተን፤ ያለዚያ የተቈጡ ሰዎች ጒዳት ላይ ይጥሉሃል፤ አንተም ቤተ ሰብህም ሕይወታችሁን ታጣላችሁ” አሉት።

26 የዳን ሰዎች ይህን ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሚካም የማይችላቸው መሆኑን በማየት ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።

27 ከዚያም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ካህኑን ወስደው ወደ ላይሽ በመሄድ፣ በሰላምና ያለ ስጋት ይኖር የነበረውን ሕዝብ በሰይፍ መቱት፤ ከተማዪቱንም በእሳት አቃጠሏት።

28 የሚኖሩት ከሲዶና በጣም ርቀው ስለ ነበርና ከማንም ጋር ግንኙነት ስላልነበራቸው የሚታደጋቸው አንድም አልነበረም፤ ከተማዪቱም የምትገኘው በቤትሮዓብ አጠገብ ነበረ።የዳንም ሰዎች ከተማዪቱን እንደ ገና ሠርተው መኖሪያቸው አደረጓት።

29 ከተማዪቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሯት፤ ቀድሞ ግን ስሟ ላይሽ ይባል ነበር።

30 እዚያም የዳን ሰዎች ለራሳቸው ጣዖታት አቆሙ፤ የሙሴ ልጅ፣ የጌርሳም ልጅ ዮናታንና የእርሱም ልጆች ምድሪቱ እስከ ተማረከችበት ጊዜ ድረስ ለዳን ነገድ ካህናት ሆኗቸው፤

31 ስለዚህም ሚካ የሠራቸውን ጣዖታት፣ የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ባለማቋረጥ አመለኳቸው።