9 ሰውየውም ከቁባቱና ከአገልጋዩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ፣ የልጅቱ አባት ዐማቱ “እነሆ ጊዜው እየመሸ ነው፤ እዚሁ እደሩ፤ ቀኑ እየተገባደደ ነው፤ እዚሁ አድራችሁ ተደሰቱ፤ ነገ ጠዋት ማልዳችሁ በመነሣት መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ” አለው።
10 ሌዋዊው ግን በዚያች ሌሊት በዚያ ለማደር ስላልፈለገ ተነሥቶ የተጫኑትን ሁለቱን አህዮቹንና ቁባቱን ይዞ ኢየሩሳሌም ወደተባለችው ወደ ኢያቡስ ሄደ።
11 ወደ ኢያቡስ እንደ ቀረቡም ጊዜው እየመሸ ስለ ነበር አገልጋዩ ጌታውን፣ “እንግዲህ ወደዚህች ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ ጐራ ብለን እንደር” አለው።
12 ጌታውም፣ “አይሆንም፤ ሕዝቧ እስራኤላዊ ወዳልሆነ ወደ ባዕድ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ አልፈን እንሂድ” አለው።
13 ቀጥሎም፣ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው።
14 ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች።
15 ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማዪቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር።