1 የእግዚአብሔር መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤
2 እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድ ነው?
3 ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስ ወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፣ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።”
4 የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ በተናገረ ጊዜ፣ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤
5 ያንን ስፍራ ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ።
6 ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ።
7 ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከእርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ።