4 የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ በተናገረ ጊዜ፣ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤
5 ያንን ስፍራ ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ።
6 ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ።
7 ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከእርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ።
8 የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ።
9 እነርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው ከገዓስ ተራራ በስተ ሰሜን ባለችው በራሱ ርስት ላይ በተምናሔሬስ ቀበሩት።
10 ያ ሁሉ ትውልድ ወደ አባቶቹ ከተከማቸ በኋላ እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ።