መሳፍንት 20:34-40 NASV

34 ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺህ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፣ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር።

35 እግዚአብሔር ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ።

36 ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ።በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለ ተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ።

37 ከዚያም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በድንገት እየተወረወሩ ወደ ጊብዓ ገቡ፤ በየቦታው ተሰራጭተውም መላዪቱን ከተማ በሰይፍ መቱ።

38 የእስራኤል ሰዎች ያሸመቀው ጦር በከተማዪቱ ውስጥ ከባድ የጢስ ደመና ምልክት እንዲያሳይ፤

39 እስራኤላውያንም ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ እንዲያፈገፍጉ ተስማሙ።ብንያማውያንን ማጥቃት እንደ ጀመሩ፣ ሠላሳ እስራኤላውያንን ስለ ገደሉ፣ “እንደ መጀመሪያው የጦርነት ጊዜ እያሸነፍናቸው ነው” አሉ።

40 ነገር ግን የጢሱ ዐምድ ከከተማዪቱ መነሣት በጀመረ ጊዜ፣ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ዞረው የመላዪቱ ከተማ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ።