መሳፍንት 21:3-9 NASV

3 እንዲህም አሉ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ ለምን በእስራኤል ላይ ሆነ? ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዴት ይታጣ?”

4 በማግሥቱ ጠዋት ሕዝቡ መሠዊያ ሠሩ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ።

5 በምጽጳ፣ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ያልተገኘ ማንኛውም ሰው መገደል አለበት ብለው እስራኤላውያን ተማምለው ስለ ነበር፣ “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን አለ?” ሲሉ ጠየቁ።

6 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያማውያን በማዘን እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ታጥቷል፤

7 ሴቶች ልጆቻችንን ለእነዚህ ብንያማውያን በጋብቻ ላንሰጥ በእግዚአብሔር ስለ ማልን ለተረፉት እንዴት ሚስት ልናገኝላቸው እንችላለን?”

8 ከዚያም፣ “ከእስራኤል ነገዶች ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን ነው” ሲሉ ጠየቁ፤ ታዲያ ከኢያቢስ ገለዓድ አንድም ሰው ለጉባኤው ወደ ሰፈሩ አለመምጣቱን ተረዱ፤

9 ሕዝቡን ሲቈጥሩም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች አንድም ሰው አልነበረምና።