መሳፍንት 6:19-25 NASV

19 ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፣ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት።

20 የእግዚአብሔር መልአክ፣ “ሥጋውንና ዕርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፣ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደታዘዘው አደረገ።

21 መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተሰወረ።

22 ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ።

23 እግዚአብሔርም፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው።

24 ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “እግዚአብሔር ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል።

25 በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል።