መሳፍንት 6:21-27 NASV

21 መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተሰወረ።

22 ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ።

23 እግዚአብሔርም፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው።

24 ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “እግዚአብሔር ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል።

25 በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል።

26 በዚህ ፍርስራሽ ጒብታ ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።”

27 ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተ ሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር።