መሳፍንት 7:7-13 NASV

7 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፣ “ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ በጠጡት ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የቀሩት በሙሉ ወደየመጡበት ይመለሱ” አለው።

8 ጌዴዎንም የቀሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ ሦስት መቶውን ግን አስቀራቸው፤ እነርሱም የሚመለሱትን ሰዎች ስንቅና መለከት ወሰዱ።በዚህ ጊዜ የምድያማውያኑ ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቆአማው ውስጥ ነበር።

9 በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ፤ በሰፈሩም ላይ ውረድ፤ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና።

10 አደጋ ለመጣል የምትፈራ ከሆነ ግን፣ ፉራ ከተባለው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤

11 የሚሉትንም አድምጥ፤ ከዚያ በኋላ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ፤” ስለዚህም ጌዴዎን አገልጋዩን ፉራን አስከትሎ እስከ ሰፈሩ ዳርቻ ወረደ።

12 ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎችም የምሥራቅ ሕዝቦች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ስፍር ቍጥር አልነበረውም።

13 አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፣ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፣ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታቱም ኀይለኛነት የተነሣ ድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር።