መሳፍንት 8:3-9 NASV

3 እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ ታዲያ እናንተ ከፈጸማችሁት ጋር የሚወዳደር ምን ማድረግ እችል ነበር?” ይህን ሲሰሙ ቍጣቸው በረደ።

4 ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር።

5 የሱኮትንም ሰዎች፣ “የምድያምንም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን በማሳደድ ላይ ስለ ሆንሁ የተከተሉኝም ሰዎች ስለ ደከሙብኝ እባካችሁ የሚበሉትን እንጀራ ስጧቸው” አላቸው።

6 የሱኮት ሹማምት ግን፣ “ለተከተሉህ ሰዎች እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዛብሄልና ስልማና በእጅህ ገብተዋልን?” አሉት።

7 ጌዴዎንም መልሶ፣ “ደህና፤ እግዚብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በምድረ በዳ እሾኽና አሜከላ ሥጋችሁን እተለትላለሁ” አላቸው።

8 ከዚያም ወደ ጵኒኤል ሰዎች ሄዶ ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የእነርሱም መልስ የሱኮት ሰዎች ከሰጡት መልስ ጋር አንድ ዐይነት ነበር።

9 እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች፣ “በድል አድራጊነት በሰላም ስመለስ ከተማችሁን የምትጠብቁበትን ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” አላቸው።