2 “የሴኬምን ነዋሪዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፤ ‘ሰባዎቹ የይሩባኣል ልጆች ቢገዟችሁ ይሻላል ወይስ አንድ ሰው ብቻ?’ የሥጋችሁ ቍራጭ፣ ያጥንታችሁ ፍላጭ መሆኔን ልብ በሉ።”
3 የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ነዋሪዎች በሙሉ ነገሩ፤ አቤሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ዳዳ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል ብለዋልና”።
4 እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል ናስ ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት።
5 ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩበኣል የመጨራሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ።
6 የሴኬምና የቤት ሚሎ ነዋሪዎች በሙሉ አቤሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ።
7 ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ የሴኬም ነዋሪዎች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ፤
8 ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።