መሳፍንት 9:3-9 NASV

3 የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ነዋሪዎች በሙሉ ነገሩ፤ አቤሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ዳዳ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል ብለዋልና”።

4 እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል ናስ ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት።

5 ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩበኣል የመጨራሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ።

6 የሴኬምና የቤት ሚሎ ነዋሪዎች በሙሉ አቤሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ።

7 ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ የሴኬም ነዋሪዎች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ፤

8 ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

9 የወይራ ዛፍም፣ “ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?” አለ።