ኢያሱ 12:1-6 NASV

1 እንግዲህ እስራኤላውያን ድል ያደረጓቸውና ከዮርዳኖስ ማዶ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን የዓረባን ክፍል በሙሉ ይዞ፣ ከአርኖን ሸለቆ እስከ አርሞንዔም ተራራ የሚዘልቀውን ግዛታቸውን የወሰዱባቸው ነገሥታት እነዚህ ናቸው፤

2 መቀመጫውን በሐሴቦን አድርጎ የገዛው የአሞራውያን ንጉሥ ሴዎን፣ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ላይ ካለችው ከአሮዔር ማለት ከሸለቆው መካከል አንሥቶ፣ የአሞናውያን ወሰን እስከ ሆነው እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ ገዝቶአል፤ ይህም የገለዓድን እኩሌታ ይጨምራል።

3 እንዲሁም ከኪኔሬት ባሕር እስከ ሙት ባሕር ያለውን ምሥራቃዊውን ዓረባ፣ እስከ ቤት የሺሞትና ከዚያም በስተ ደቡብ እስከ ፈስጋ ተራራ ግርጌ ድረስ ገዝቶአል።

4 መቀመጫውን በአስታሮትና በኤድራይ አድርጎ የገዛውና ከመጨረሻዎቹ ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነው የባሳን ንጉሥ ዐግ፣

5 የአርሞንዔምን ተራራ፣ ሰልካንን፣ ባሳንን ሁሉ እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ድንበሮች እንዲሁም ከገለዓድ እኩሌታ እስከ ሐሴቦን ንጉሥ እስከ ሴዎን ወሰን ድረስ ገዝቶአል።

6 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴና እስራኤላውያን እነዚህን ድል አደረጉ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴም ምድራቸውን ለሮቤል፣ ለጋድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርጎ ሰጣቸው።