ኢያሱ 14:3-9 NASV

3 ሙሴ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው፣ የዮርዳኖስን ምሥራቅ ክፍል ርስት አድርጎ ሰጣቸው፤ ሌዋውያኑ ግን አብረዋቸው እንዲካፈሉ አላደረገም፤

4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ሆነው ነበርና፤ ለሌዋውያኑ ግን ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለበግ፣ ለፍየልና ለከብት መንጎቻቸው መሰማሪያ እንዲሆን አብሮ የተከለለላቸውን ምድር ብቻ እንጂ ሌላ አልሰጣቸውም፤

5 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ምድሪቱን ተካፈሉ።

6 የይሁዳም ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከዚያም የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ ስለ አንተና ስለ እኔ፣ የአምላክ ሰው ለሆነው ለሙሴ የተናገረውን ታውቃለህ።

7 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም ትክክለኛውን ማስረጃ ይዤለት መጣሁ፤

8 አብረውኝ ወደዚያ የወጡት ወንድሞቼ ግን፣ የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ ሆኖም እኔ አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት።

9 ስለዚህም ሙሴ በዚያች ዕለት፣ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ተከትለኸዋልና እግርህ የረገጣት ምድር ለዘላለም የአንተና የዘርህ ርስት ትሆናለች’ ብሎ ማለልኝ።