ኢያሱ 14:4-10 NASV

4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ሆነው ነበርና፤ ለሌዋውያኑ ግን ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለበግ፣ ለፍየልና ለከብት መንጎቻቸው መሰማሪያ እንዲሆን አብሮ የተከለለላቸውን ምድር ብቻ እንጂ ሌላ አልሰጣቸውም፤

5 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ምድሪቱን ተካፈሉ።

6 የይሁዳም ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከዚያም የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ ስለ አንተና ስለ እኔ፣ የአምላክ ሰው ለሆነው ለሙሴ የተናገረውን ታውቃለህ።

7 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም ትክክለኛውን ማስረጃ ይዤለት መጣሁ፤

8 አብረውኝ ወደዚያ የወጡት ወንድሞቼ ግን፣ የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ ሆኖም እኔ አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት።

9 ስለዚህም ሙሴ በዚያች ዕለት፣ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ተከትለኸዋልና እግርህ የረገጣት ምድር ለዘላለም የአንተና የዘርህ ርስት ትሆናለች’ ብሎ ማለልኝ።

10 “አሁንም እነሆ፤ ልክ እግዚአብሔር እንዳለው ይህን ለሙሴ ከተናገረበት ጊዜ አንሥቶ እስራኤል በምድረ በዳ ሲንከራተት እኔን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት ጠብቆ አኑሮኛል፤ ይኸው ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ።