ኢያሱ 2:1-7 NASV

1 ከዚያም የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ ምድሪቱን፣ በተለይም የኢያሪኮን ከተማ ሰልሉ” ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ፤ ሰዎቹም ሄደው ረዓብ ከተባለች ጋለ ሞታ ቤት ገቡ፤ በዚያም ዐደሩ።

2 ለኢያሪኮም ንጉሥ፣ “እነሆ፤ ምድሪቱን ሊሰልሉ ጥቂት እስራኤላውያን በሌሊት ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ተነገረው።

3 የኢያሪኮም ንጉሥ፣ “ወደ አንቺ መጥተው ወደ ቤትሽ የገቡት ሰዎች ምድሪቱን በሙሉ ለመሰለል ስለ ሆነ፣ እንድታስወጪአቸው” የሚል መልእክት ወደ ረዓብ ላከ።

4 ሴቲቱ ግን ሁለቱን ሰዎች ተቀብላ ሸሽጋቸው ስለ ነበር፣ እንዲህ አለች፤ “በእርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጡ አላውቅም።

5 ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል፤ በየት በኩል እንደሄዱ ግን እኔ አላውቅም፤ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁና ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው።”

6 ነገር ግን ሰዎቹን ጣራ ላይ አውጥታ በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር።

7 ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሄዱ፣ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደሄዱም የቅጥሩ በር ተዘጋ።