ኢያሱ 22:20-26 NASV

20 የዛራ ልጅ አካን፣ እርም የሆነውን ነገር በመውሰድ ኀጢአት ስለ ሠራ፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ላይ ቍጣ አልመጣምን? በሠራው ኀጢአት የሞተውም እርሱ ብቻ አልነበረም።”

21 ከዚያም የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል ጐሣ መሪዎች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤

22 “ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር! ኀያሉ አምላክ፤ እግዚአብሔር! እርሱ ያውቃል! እስራኤልም ይህን ይወቅ! ይህ የተደረገው በማመፅ ወይም ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ከሆነ፣ ዛሬ አትማሩን!

23 መሠዊያውን የሠራነው እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ለማለት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ልናሳርግበት ወይም የኅብረት መሥዋዕት ልናቀርብበት አስበን ከሆነ፣ ራሱ እግዚአብሔር ይበቀለን።

24 “እኛማ ይህን ያደረግነው፣ ወደ ፊት ዘሮቻችሁ ለዘሮቻችን እንዲህ እንዳይሏቸው ፈርተን ነው፤ “ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን ግንኙነት አላችሁ?

25 እናንት የሮቤልና የጋድ ልጆች፤ እግዚአብሔር ዮርዳኖስን በመካከላችን መለያ ድንበር ስላደረገው፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም።’ ስለዚህ ዘሮቻችሁ፣ የእኛ ዘር እግዚአብሔርን እንዳይፈራ ሊያደርጉ ይችላሉ።

26 “እኛም ‘እንነሣና መሠዊያ እንሥራ፤ የምንሠራው መሠዊያ ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ አይውልም’ ያልነው ለዚህ ነው።