ኢያሱ 6:18-24 NASV

18 እናንተ ግን እርም ከሆኑት ነገሮች አንዳች በመውሰድ በራሳችሁ ላይ ጥፋት እንዳታመጡ እጃችሁን ሰብስቡ፤ ያለዚያ የእስራኤልን ሰፈር ለጥፋት ትዳርጋላችሁ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስበትም ታደርጋላችሁ፤

19 ብሩና ወርቁ እንዲሁም የናሱና የብረቱ ዕቃ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስለ ሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት ይግባ።”

20 መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ፤ የመለከቱ ድምፅ ተሰምቶ፣ ሕዝቡ በኀይል ሲጮኽ ቅጥሩ ፈረሰ፤ እያንዳንዱ ሰው ሰተት ብሎ ገባ፤ ከተማዪቱም በእጃቸው ወደቀች።

21 በከተማዪቱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ማለትም ወንዱንና ሴቱን፣ ወጣቱንና ሽማግሌውን፣ ከብቱንና በጒን እንዲሁም አህያውን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።

22 ኢያሱ ምድሪቱን የሰለሉትን ሁለቱን ሰዎች፣ “ወደ ጋለሞታዪቱ ቤት ሂዱ፤ በማላችሁላትም መሠረት እርስዋንና የእርሷ የሆነውን ሁሉ ከዚያ አውጡ” አላቸው።

23 ስለዚህ ሁለቱ ወጣት ሰላዮች ገብተው ረዓብን፣ አባቷንና እናቷን፣ ወንድሞቿንና የእርሷ የሆኑትን ሁሉ ከዚያ አወጧቸው። ቤተ ዘመዶቿንም ሁሉ አውጥተው ከእስራኤል ሰፈር ውጭ አስቀመጧቸው።

24 ከዚያም ከተማዪቱን በሙሉ፣ በውስጧ ያለውንም ሁሉ አቃጠሉ፤ ብሩንና ወርቁን፣ የናሱንና የብረቱን ዕቃ ግን በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አኖሩ።