ኢያሱ 7:18-24 NASV

18 ኢያሱ የዘንበሪን ቤተ ሰብ አባላት አንድ በአንድ ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም ከይሁዳ ነገድ የሆነውም የዛራ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የከርሚ ልጅ አካን ለብቻው ተለየ።

19 ኢያሱም አካንን፣ “ልጄ ሆይ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ፤ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውን ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው።

20 አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እውነት ነው! የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ፤ ያደረግሁትም ይህ ነው፤

21 ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ አምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሮአል።”

22 በዚህ ጊዜ ኢያሱ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ በዚያም ብሩ ከታች ሆኖ ዕቃው እንደ ተቀበረ አገኙ።

23 ከድንኳኑም አውጥተው፣ ኢያሱና እስራኤላውያን ሁሉ ወዳሉበት አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩ።

24 ኢያሱም ከመላው እስራኤል ጋር ሆኖ፣ የዛራን ልጅ አካንን፣ ብሩን፣ ካባውን፣ የወርቁን ቡችላ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ የከብቱን መንጋ፣ አህዮቹንና በጎቹን እንዲሁም ድንኳኑንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ወደ አኮር ሸለቆ አስወሰደ።