ኢያሱ 7:20-26 NASV

20 አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እውነት ነው! የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ፤ ያደረግሁትም ይህ ነው፤

21 ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ አምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሮአል።”

22 በዚህ ጊዜ ኢያሱ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ በዚያም ብሩ ከታች ሆኖ ዕቃው እንደ ተቀበረ አገኙ።

23 ከድንኳኑም አውጥተው፣ ኢያሱና እስራኤላውያን ሁሉ ወዳሉበት አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩ።

24 ኢያሱም ከመላው እስራኤል ጋር ሆኖ፣ የዛራን ልጅ አካንን፣ ብሩን፣ ካባውን፣ የወርቁን ቡችላ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ የከብቱን መንጋ፣ አህዮቹንና በጎቹን እንዲሁም ድንኳኑንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ወደ አኮር ሸለቆ አስወሰደ።

25 ኢያሱም፣ “እንዲህ ያለውን መከራ ለምን አመጣብህን? እነሆ፤ ዛሬ በአንተም ላይ እግዚአብሔር መከራ ያመጣብሃል” አለው።ከዚያም እስራኤል በሙሉ በድንጋይ ወገሩት፤ የቀሩትንም እንደዚሁ ከወገሩ በኋላ በእሳት አቃጠሏቸው።

26 በአካንም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታየውን ታላቅ የድንጋይ ቊልል ከመሩበት፤ ከዚያም እግዚአብሔር ከአስፈሪ ቊጣው ተመለሰ፤ ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያ ስፍራ የአኮር ሸለቆ ተባለ።