ኢዮብ 18 NASV

በልዳዶስ

1 ሹሐዊው በልዳዶስ እንዲህ ሲል መለሰ፤

2 “ይህን ንግግር የምትጨርሰው መቼ ነው?እስኪ ልብ ግዛ፤ ከዚያ በኋላ እንነጋገራለን።

3 ለምን እንደ ከብት መንጋ እንቈጠራለን?እንደ ደንቈሮስ ለምን ታየናለህ?

4 አንተ በቍጣ የነደድህ እንደሆነ፣ምድር ባዶዋን ትቀራለች?ወይስ ዐለት ከሥፍራው ተነቅሎ ይወሰዳል?

5 “የክፉዎች መብራት ይጠፋል፤የእሳቱም ነበልባል ድርግም ይላል።

6 የድንኳኑ ብርሃን ይጨልማል፤መብራቱም በላዩ ይጠፋል፤

7 የርምጃው ብርታት ይደክማል፤የገዛ ዕቅዱም ይጥለዋል።

8 እግሩ በወጥመድ ይያዛል፤በመረብም ይተበተባል።

9 አሽክላ ተረከዙን ይይዘዋል፤ወስፈንጥርም ያጣብቀዋል።

10 በምድር ላይ የሸምበቆ ገመድ፣በመንገዱም ላይ ወጥመድ በስውር ይቀመጥለታል።

11 ድንጋጤ በዙሪያው ያስፈራራዋል፤ተከትሎም ያሳድደዋል።

12 መቅሠፍት ሊውጠው ቀርቦአል፤ጥፋትም የእርሱን ውድቀት ይጠባበቃል።

13 ደዌ ቈዳውን ይበላል፤የሞት በኵርም ቅልጥሙን ይውጣል።

14 ተማምኖ ከሚኖርበት ድንኳን ይነቀላል፤ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ይነዳል።

15 ድንኳኑ በእሳት ይያያዛል፤በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል።

16 ሥሩ ከታች ይደርቃል፤ቅርንጫፉም ከላይ ይረግፋል።

17 መታሰቢያው ከምድር ገጽ ይጠፋል፤ስሙም በአገር አይነሣም።

18 ከብርሃን ወደ ጨለማ ይጣላል፤ከዓለምም ይወገዳል።

19 በሕዝቡ መካከል ልጅ ወይም ዘር አይኖረውም፤በኖረበትም አገር ተተኪ አያገኝም።

20 ባጋጠመው ሁኔታ የምዕራብ ሰዎች ይደነግጣሉ፤የምሥራቅም ሰዎች በፍርሀት ይዋጣሉ።

21 በርግጥ የክፉ ሰው መኖሪያ፣እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው መድረሻ ይህ ነው።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42