ኢዮብ 21 NASV

ኢዮብ

1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤

2 “ቃሌን በጥንቃቄ ስሙ፤የምታጽናኑኝም በዚህ ይሁን፤

3 ንግግሬን በትዕግሥት አድምጡ፤ከተናገርሁ በኋላ፣ መሣለቅ ትችላላችሁ።

4 “በውኑ ቅርታዬ በሰው ላይ ነውን?ትዕግሥት ማጣትስ አይገባኝምን?

5 ተመልከቱኝና ተገረሙ፤አፋችሁን በእጃችሁ ለጒሙ።

6 ስለዚህ ነገር ባሰብሁ ቍጥር እደነግጣለሁ፤ሰውነቴም በፍርሀት ይንቀጠቀጣል።

7 ኀጢአተኞች ለምን በሕይወት ይኖራሉ?ለምን ለእርጅና ይበቃሉ? ለምንስ እያየሉ ይሄዳሉ?

8 ዘራቸው በዐይናቸው ፊት፣ልጆቻቸውም በዙሪያቸው ጸንተው ሲኖሩ ያያሉ፤

9 ቤታቸው ያለ ሥጋት በሰላም ይኖራል፤የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።

10 ኮርማቸው ዘሩ በከንቱ አይወድቅም፤ያስረግዛል፤ ላማቸውም ሳትጨነግፍ ትወልዳለች።

11 ልጆቻቸውን እንደ በግ መንጋ ያሰማራሉ፤ሕፃናታቸውም ይቦርቃሉ።

12 በከበሮና በክራር ይዘፍናሉ፤በዋሽንትም ድምፅ ይፈነጫሉ።

13 ዕድሜያቸውን በተድላ ያሳልፋሉ፤በሰላምም ወደ መቃብር ይወርዳሉ።

14 እግዚአብሔርንም እንዲህ ይሉታል፤ ‘አትድረስብን!መንገድህንም ማወቅ አንፈልግም።

15 እናገለግለው ዘንድ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ ማን ነው?ወደ እርሱ ብንጸልይስ ምን እናገኛለን?’

16 ይሁንና ብልጽግናቸው በእጃቸው አይደለም፤ከኀጢአተኞች ምክር እርቃለሁ።

17 “የኀጢአተኞች መብራት የጠፋው ስንት ጊዜ ነው?የእግዚአብሔር ቍጣ መከራ የመጣባቸው፣መቅሠፍትም የደረሰባቸው ስንት ጊዜ ነው?

18 በነፋስ ፊት እንዳለ ገለባ፣በዐውሎ ነፋስም እንደ ተወሰደ ዕብቅ የሆኑት ስንት ጊዜ ነው?

19 እናንተ፣ ‘እግዚአብሔር የሰውን ቅጣት ለልጆቹ ያከማቻል’ ትላላችሁ፤ነገር ግን ያውቀው ዘንድ ለሰውየው ለራሱ ይክፈለው፤

20 ዐይኖቹ የራሱን ውድቀት ይዩ፤ሁሉን ከሚችል አምላክ ቍጣ ይጠጣ።

21 ሰው ወራቱ በተገባደደ ጊዜ፣ለቀሪ ቤተ ሰቡምን ይገደዋል?

22 “ከፍ ባሉት ላይ ለሚፈርድ አምላክ፣ዕውቀትን ሊያስተምረው የሚችል አለን?

23 አንድ ሰው በፍጹም ተድላ ደስታ እየኖረ፣በሙሉ ብርታቱም እያለ ይሞታል፤

24 ሰውነቱ በምቾት፣ዐጥንቱም በስብ ተሞልቶ እያለ በሞት ይለያል።

25 ሌላው ሰው ደግሞ አንዳች መልካም ነገር ሳያይ፣በተመረረች ነፍስ ይሞታል፤

26 ሁለቱም በዐፈር ውስጥ አንድ ላይ ይተኛሉ፤ትልም ይወርሳቸዋል።

27 “እነሆ፣ ምክራችሁን፣በእኔ ላይ ያሤራችሁትንም ተረድቻለሁ።

28 እናንተ፣ ‘የትልቁ ሰው ቤት፣ኀጢአተኛውም የኖረበት ድንኳን የት አለ?’ አላችሁ፤

29 መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን?የነገሯችሁንስ ነገር በጥሞና አላዳመጣችሁምን?

30 ክፉ ሰው በመቅሠፍት ቀን እንደሚጠበቅ፣በቍጣም ቀን እንደሚተርፍ አታውቁምን?

31 ተግባሩን ፊት ለፊት የሚነግረው ማን ነው?የእጁንስ ማን ይሰጠዋል?

32 ወደ መቃብር ይወስዱታል፤ለመቃብሩም ጠባቂ ይደረግለታል።

33 የሸለቈው ዐፈር ምቹ ይሆንለታል፤ሰው ሁሉ ይከተለዋል፤ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝብ በፊቱ ይሄዳል።

34 “መልሳችሁ ከሐሰት በስተቀር ሌላ አይገኝበትም፤ታዲያ፣ በማይረባ ነገር እንዴት ልታጽናኑኝ ትችላላችሁ!”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42