ኢዮብ

ምዕራፎች 4

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኤልፋዝ

1ቴማናዊው ኤልፋዝም እንዲህ ሲል መለሰ፤ 2“አንድ ሰው ከአንተ ጋር ለመናገር ቢሞክር፣ ቅር ይልሃልን?ዳሩ ግን ከመናገር ማን ሊቈጠብ ይችላል? 3እነሆ፤ አንተ ብዙዎችን ታስተምር እንደ ነበር አስብ፤የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፤ 4ቃልህ የተሰናከሉትን ያነሣ ነበር፤የሚብረከረከውንም ጒልበት ታጸና ነበር። 5አሁን ግን መከራ አገኘህ፣ አንተም ተስፋ ቈረጥህ፤ሸነቈጠህ፤ ደነገጥህም። 6እግዚአብሔርን መፍራት መታመኛህ፣ቀና አካሄድህም ተስፋህ አይደለምን? 7“አሁንም አስተውል፤ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ፣ ማን ነው?ቅኖችስ መች ተደምስሰው ያውቃሉ? 8እኔ እንዳየሁ፣ ክፋትን የሚያርሱ፣መከራንም የሚዘሩ ያንኑ ያጭዳሉ። 9በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፤በቍጣውም ወላፈን ይደመሰሳሉ። 10አንበሳ ያገሣል፤ ቍጡውም አንበሳ ይጮኻል፤የደቦል አንበሳው ጥርስ ግን ተሰብሮአል። 11ብርቱው አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፤የአንበሳዪቱም ግልገሎች ይበተናሉ። 12“ቃል በምስጢር መጣልኝ፤ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች። 13በሚያስጨንቅ የሌሊት ሕልም ውስጥ፣ከባድ እንቅልፍም በሰዎች ላይ በወደቀ ጊዜ፣ 14ፍርሀትና መንቀጥቀጥ ያዘኝ፤ዐጥንቶቼም ሁሉ ተናወጡ። 15መንፈስ ሽው ብሎ በፊቴ አለፈ፤የገላዬም ጠጒር ቆመ። 16እርሱም ቆመ፣ምን እንደሆነ ግን መለየት አልቻልሁም፤አንድ ቅርጽ በዐይኔ ፊት ነበረ፤በእርጭታ ውስጥ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፤ 17‘ሥጋ ለባሽ ከእግዚአብሔር ይልቅ ጻድቅ ሊሆን ይችላልን?ሰውስ ከፈጣሪው ይልቅ ንጹሕ ሊሆን ይችላልን? 18እግዚአብሔር በአገልጋዮቹ ላይ እምነት ካልጣለ፣መላእክቱንም በስሕተታቸው ከወቀሰ፤ 19ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፣መሠረታቸው ከዐፈር የሆነ፣ከብልም ይልቅ በቀላሉ የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ? 20በንጋትና በምሽት መካከል ይደቃሉ፤ሳይታሰብም ለዘላለም ይጠፋሉ።