ኢዮብ 20 NASV

ሶፋር

1 ናዕማታዊውም ሶፋር እንዲህ ሲል መለሰ፤

2 “እጅግ ታውኬአለሁና፣ሐሳቤ መልስ እንድሰጥ ይጐተጒተኛል።

3 የሚያቃልለኝን ንግግር ሰምቼአለሁ፤መልስም እሰጥ ዘንድ መንፈሴ ገፋፋኝ።

4 “ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ ጊዜ ጀምሮ፣ከጥንቱ እንዴት እንደ ነበረ ታውቃለህን?

5 የኀጢአተኞች መፈንጨት ለአጭር ጊዜ፣የክፉዎችም ደስታ ለቅጽበት መሆኑን አታውቅምን?

6 እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ቢልም፣ዐናቱም ደመናትን ቢነካ፣

7 እንደ ኵበት ለዘላለም ይጠፋል፤ቀድሞ ያዩትም፣ ‘የት ገባ?’ ይላሉ።

8 እንደ ሕልም በሮ ይጠፋል፤ አይገኝምም፤እንደ ሌሊትም ራእይ በቅጽበት ያልፋል።

9 ቀድሞ ያየው ዐይን ዳግመኛ አያየውም፤የነበረበትም ቦታ ከእንግዲህ አይመለከተውም።

10 ልጆቹ ለድኾች ካሣ መክፈል አለባቸው፤እጆቹም ሀብቱን መልሰው መስጠት ይገባቸዋል።

11 ዐጥንቱን የሞላው የወጣትነት ብርታት፣ከእርሱ ጋር በዐፈር ውስጥ ይተኛል።

12 “ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፣ከምላሱም በታች ቢደብቀው፣

13 አውጥቶ ለመጣል እየሳሳ፣በአፉ ውስጥ ቢያቈየው፣

14 ምግቡ በሆዱ ውስጥ ይመራል፤በውስጡም እንደ እባብ መርዝ ይሆናል።

15 የዋጠውን ሀብት ይተፋል፤እግዚአብሔርም መልሶ ከሆዱ ያወጣዋል።

16 የእባብ መርዝ ይጠባል፤የእፉኝትም ምላስ ይገድለዋል።

17 ማርና ቅቤ በሚያፈሱ ጅረቶች፣በወንዞችም አይደሰትም።

18 የለፋበትን ሳይበላው ይመልሳል፤ከንግዱም ባገኘው ትርፍ አይደሰትም፤

19 ድኾችን በመጨቈን ባዶአስቀርቶአቸዋልና፣ ያልሠራውንም ቤት ነጥቆአል።

20 “ክፉ ምኞቱ ዕረፍት አይሰጠውምሀብቱም ሊያድነው አይችልም።

21 ያለውን አሟጦ ስለሚበላ፣ዘላቂ ብልጽግና አይኖረውም።

22 በተድላ መካከል እያለ ጒስቍልና ይመጣበታል፤በከባድ መከራም ይዋጣል።

23 ሆዱን በሞላ ጊዜ፣እግዚአብሔር የሚነድ ቍጣውን ይሰድበታል፤መዓቱንም ያወርድበታል።

24 ከብረት መሣሪያ ቢሸሽም፣የናስ ቀስት ይወጋዋል።

25 ቀስቱን ከጀርባው፣የሚያብለጨልጨውንም ጫፍ ከጒበቱ ይመዛል፤ፍርሀትም ይይዘዋል፤

26 ሀብቱ ለድቅድቅ ጨለማ ተዳርጎአል፤ሰው ባላራገበው እሳት ይበላል፤በድንኳኑም ውስጥ የተረፈውን ይልሳል።

27 ሰማያት ኀጢአቱን ይገልጡበታል፤ምድርም ትነሣበታለች፤

28 በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን ቤቱን ጐርፍ፣መኖሪያውንም ወራጅ ውሃ ይወስድበታል።

29 እግዚአብሔር ለኀጢአተኞች የወሰነው ዕድል ፈንታ፣ከአምላክም ዘንድ የተመደበላቸው ቋሚ ቅርስ ይህ ነው።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42