1 ኤሊሁ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤
2 “ ‘በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ነኝ’ ማለትህ፣ትክክል ይመስልሃልን?
3 ደግሞ ‘ያገኘሁት ጥቅም ምንድን ነው?ኀጢአት ባለ መሥራቴስ ምን አተረፍሁ?’ ብለህ ጠይቀኸዋል።
4 “ለአንተና አብረውህ ላሉት ባልንጀሮችህ፣መልስ መስጠት እፈልጋለሁ።
5 ቀና ብለህ ወደ ሰማይ እይ፤ከአንተ በላይ ከፍ ብለው ያሉትንም ደመናት ተመልከት።
6 ኀጢአትህስ ቢበዛ እርሱን ምን ትጐዳዋለህ?ኀጢአትህስ ቢበዛ ምን ያደርገዋል?
7 ጻድቅ ብትሆንም ለእርሱ ምን ትሰጠዋለህ?ከእጅህስ ምን ይቀበላል?
8 ክፋትህ የሚጐዳው እንዳንተ ያለውን ሰው ብቻ ነው፤ጽድቅህም የሚጠቅመው የሰውን ልጆች ብቻ ነው።
9 “ሰው ከጭቈና ብዛት የተነሣ ይጮኻል፤ከኀያሉም ክንድ ሥር ለመውጣት ለርዳታ ይጣራል።
10 ነገር ግን እንዲህ የሚል የለም፤ ‘ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው?በሌሊት መዝሙርን የሚሰጥ፣
11 ከምድር እንስሳት ይልቅ የሚያስተምረን፣ከሰማይ ወፎችም ይልቅ ጠቢባን የሚያደርገን፣ እርሱ የት አለ?’
12 ከዐመፀኞች ትዕቢት የተነሣ፣ሰዎች ሲጮኹ አይመልስላቸውም፤
13 በእርግጥ እግዚአብሔር ከንቱ ጩኸታቸውን አይሰማም፤ሁሉን የሚችል አምላክ አያዳምጣቸውም።
14 ጒዳይህን ፊቱ አቅርበህ፣ብዙ ጠብቀኸው፣ግን እንዳላየኸው ስትናገር፣ታዲያ፣ አንተን እንዴት ይስማህ!
15 ደግሞም፣ ቍጣው ቅጣት እንደማያስከትል፣ኀጢአትንም ከቍጥር እንደማያስገባ ተናግረሃል።
16 ስለዚህ ኢዮብ አፉን በከንቱ ይከፍታል፤ዕውቀት አልባ ቃላትም ያበዛል።”