ዘሌዋውያን 1:2-8 NASV

2 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከእንስሳ ወገን መባ በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ፣ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ።

3 “ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከላሞች መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያቅርበው።

4 የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል።

5 ወይፈኑን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን አምጥተው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት።

6 እርሱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም ያውጣው።

7 የካህኑ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ ዕንጨት ረብርበው እሳት ያንድዱበት።

8 ካህናቱ የአሮን ልጆች ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምረው ብልቶቹን በመሠዊያው ላይ በሚነደው ዕንጨት ላይ ይደርድሩት፤