4 በቈዳው ላይ ያለው ቋቁቻ ነጭ ሆኖ ቢታይ ነገር ግን ከቈዳው በታች ዘልቆ ባይገባና በቦታው ላይ የሚገኘው ጠጒር ወደ ነጭነት ባይለወጥ፣ ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው።
5 በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቊስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው።
6 በሰባተኛው ቀን ካህኑ እንደ ገና ይመርምረው፤ ቊስሉ ከከሰመና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቊስሉ ችፍታ እንጂ ሌላ አይደለም። ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።
7 ራሱን ለካህን አሳይቶ መንጻቱ ከታወቀ በኋላ፣ ችፍታው በቈዳው ላይ እየተስፋፋ ከሆነ፣ እንደ ገና ካህኑ ፊት ይቅረብ፤
8 ካህኑም ይመርምረው፤ ችፍታው በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ከተገኘ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።
9 “ማንኛውም ሰው ተላላፊ የቈዳ በሽታ ከያዘው፣ ወደ ካህኑ ያምጡት፤
10 ካህኑም ይመርምረው፤ በሰውነቱ ላይ ጠጒሩን ወደ ነጭነት የለወጠ ነጭ ዕባጭ ካለና በዕብጠቱም ውስጥ ቀይ ሥጋ ቢታይ፣