44 ሰውየው ደዌ አለበት፤ ርኵስም ነው፤ በራሱ ላይ ካለው ቊስል የተነሣም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ።
45 “እንዲህ ያለ ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የተቀደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጒሩን ይግለጥ፤ እስከ አፍንጫውም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ ርኩስ ነኝ’ እያለ ይጩኽ።
46 ተላላፊ በሽታው እስካለበት ጊዜ ድረስ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጥ፤ ከሰፈር ውጪም ይኑር።
47 “ከበግ ጠጒር ወይም ከበፍታ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት ልብስ በተላላፊ በሽታ ቢበከል፣
48 በሸማኔ ዕቃ ወይም በእጅ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት የበግ ጠጒር ወይም የበፍታ ልብስ፣ ወይም ማንኛውም ቈዳ ወይም ከቈዳ የተሠራ ነገር ቢሆን፣
49 በልብስ ወይም በዐጐዛ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራ ወይም በእጅ በተጠለፈ ወይም ከቈዳ በተሠራ ዕቃ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት፣ እየሰፋ የሚሄድ ተላላፊ በሽታ ስለ ሆነ ካህኑ ይየው።
50 ካህኑ ደዌውን ይመርምር፤ በደዌ የተበከለውንም ዕቃ ሰባት ቀን ያግልል።