4 የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፤ በሰውነቱ ላይ የሚያርፈውን ከበፍታ የተሠራውን የውስጥ ሱሪ ያጥልቅ፤ የበፍታውን መታጠቂያ ይታጠቅ፤ የበፍታውን መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ ልብሶቹ የተቀደሱ በመሆናቸው እነዚህን ከመልበሱ በፊት ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ።
5 ከእስራኤል ማኅበረሰብ ለኀጢአት መሥዋዕት ሁለት ተባዕት ፍየሎች፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ።
6 “አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ፣ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤
7 ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቁማቸው።
8 አሮንም አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ)፣ ሌላውን ለሚለቀቀው ፍየል ለማድረግ በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጣል።
9 በዕጣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የደረሰውንም ፍየል አምጥቶ ለኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ይሠዋ።
10 ወደ ምድረ በዳ ተለቅቆ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ፣ እንዲለቀቅ ዕጣ የወጣበትን ፍየል ከነሕይወቱ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ።