15 እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡትን የተቀደሰ መሥዋዕት ካህናቱ አያርክሱት፤
16 ይህንኑ የተቀደሰ መሥዋዕት እንዲበሉና ቅጣት የሚያስከትል በደል እንዲፈጽሙ አያድርጉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
17 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
18 “ለአሮን፣ ለልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ከእናንተ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ቢሆን፣
19 መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው ከላም ወገን ወይም ከበጎች ወይም ከፍየሎች እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ።
20 እንከን ያለበትን ማንኛውንም ነገር አታቅርቡ፤ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት አይኖረውምና።
21 ማንኛውም ሰው ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ከላም ወይም ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት ሲያቀርብ፣ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ፍጹም የሆነውንና ነውር የሌለበትን ያቅርብ።